Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በወቅታዊ የጤና ጉዳዮች ላይ ሳምንታዊ ውይይት አካሂዷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል መንግስት የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በየሳምንቱ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ላይ ምክክር የሚያደርግበት እና ምላሽ የሚሰጥበት የድንገተኛ አደጋዎች ኦፕሬሽን ማዕከል(EOC) የተግባር ውይይት ከዞንና ከልዩ ወረዳዎች ጋር በበይነ መረብ አድርጓል፡

ሳምንታዊ የአፈጻጸም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በሳምንቱ 46,815 ሰዎች የወባ በሽታ ምርመራ ማድረጋቸውንና 17,304 ሰዎች የወባ በሽታ ተገኝቶባቸው ህክምና ማግኘታቸውን የቀረበው ሪፖርት ያስረዳል።

አመራሩን ጨምሮ 4,335 ሰዎች የተሳተፉበት የወባ ንቅናቄ ስራ በየአካባቢው እስከታችኛው መዋቅር ተግባራዊ መደረጉንና ከፍተኛ የወባ ጫና ባለባቸው 366 ቀበሌዎች የተጠናከረ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የወባ በሽታ መከ/መቆጣጠር፣ የወባ ምርመራና ህክምና አገ/ት ክትትል፣ የመድሀኒት እንዲሁም የግብዓት ስርጭት እና የላብራቶሪ ምርመራ አገ/ት ጥራትን የማስጠበቅ ስራ ከክልሉ ከወረዱ የአመራር እና የባለሙያ ድጋፋዊ ክትትል ቡድን በመታገዝ ተግባራት እየተሳለጡ መሆኑንና በቀጣይም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች አንደሆኑ ከቀረበው መመልከት ተችሏል።

የኩፍኝ በሽታ፣ የተወሳሰቡ የምግብ እጥረት ችግሮች እና ሌሎች በክልሉ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ሊሆኑ የሚችሉ የጤና ጉዳዮች በመለየት የተሰሩ የምላሽ ስራዎችም በሪፖርቱ ተካተዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ አሰጣጥ ማሳላጫ ማዕከል ለወረርሽኝ የማይበገር የጤና ስርዓት ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ ከማበርከቱ ባሻገር የጤናው ሴክተር ከሌሎች ሴክተር መ/ቤቶች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ተግባራትን በዘላቂነት ተቋማዊ በሆነ መንገድ ለማስተሳሰር የሚያበረክተው አስዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ተግባር ላይ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል የሁሉንም አመራርና ማህበረሰብ ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን ከግንዛቤ ያስገባ ስራ በመፈጸም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አቶ ሳሙኤል አክለዋል፡፡

የወባ በሽታ ጫና አየጨመረ ያለባቸው የክልሉ አካባቢዎች የበሽታውን ጫና ለመቀነስ እየተደረገ ያለውን ጥረት እስከ ታችኛው መዋቅር እስከ ቀበሌ ድረስ አጠናክረው ሊያስቀጥሉ ይገባል ያሉት ኃላፊው አገ/ት የማይሰጡ የጤና ተቋማትን በመለየት አገ/ት መስጠት ወደሚችሉበት ደረጃ ማሻገር እንደሚገባ በመጠቆም የአየር ንብረት ለውጡን ታሳቢ ያደረገ የወባ በሽታ መከ/መቆ ተግባር ሊተኮርበት እንደሚገባ በማስገንዘብ በማስረጃ ላይ የተመሰረተ መረጃ ልውውጥ ስርዓቱን በማሳለጥ የወባ በሽታ በማህበረሰቡ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ማህበራዊ ፖለቲካዊ እና ኢኪኖሚያዊ ቀውስ ለማስቀረት የጋራ ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በበኩላቸው በዞን ደረጃ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ማሳለጫ ማዕከላት ወቅቱን በጠበቀ መልኩ ተግባራትን በመገምገም ድክመትና ተግዳሮቶችን በመለየት መፍትሄ የመስጠት ስራዎችን መፈጸም እንደሚገባ ገልጸዋል።

በዕቅድ ላይ መሰረት ያደረገ የድጋፍና ክትትል ስራን አስተሳስሮ መሄድ ተገቢ መሆኑን ያመላከቱት አቶ ማሙሽ በአፈጻጸም ወቅት የተስተዋሉ ጉድለቶችን ማረም እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ተግባራት ከዘመቻ ባሻገር የዕለት ተዕለት ክትትል ሊደረግባቸው እንደሚገባ ያመላከቱት ዋና ዳይሬክተሩ በጤና ኬላ የሚሰጠውን የወባ ምርመራና ህክምና አገ/ት መፈተሽ ተገቢ መሆኑን በመግለጽ የወባ ንቅናቄ ተግባራት እስከ ቀበሌ ድረስ ቀጣይነት ባለው መልኩ ሊተገበሩ ይገባል ብለዋል።

የማ/ኢት/ክልል መንግስት ጤና ቢሮ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *