የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል የዝግጁነት ዳይሬክቶሬት ከኢንስቲትዩቱ ብሔራዊ የስልጠና ማዕከል ጋር በመተባበር ከደቡብ እና ማዕከላዊ ኢትዮዽያ ተውጣጥተው በሶስት ዙር የተሰጠውን መሰረታዊ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና (Frontline-FETP) ያጠናቀቁ 27 የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች ዛሬ ጥቅምት 3/2017 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ አስመረቀ፡፡
አቶ አወል ዳውድ የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ባለሙያ እና የስልጠናው አስተባባሪ እንደገለጹት ሰልጣኞቹ ለምርቃት የበቁት ተከታታይ ሶስት ዙር ስልጠናዎችን እጠናቀውና በቡድን የሰሩት የተግባር ስራዎች ቀርበውና ተገምግመው ነው።
አቶ አወል አያይዘው እንዳብራሩት መሰረታዊ የኮምፒውተር እውቀት፣ የቅኝት መረጃን (Surveillance data) በመጠቀም ወረርሽኝ በአንድ አካባቢ ሲከሰት ቶሎ በመለየት ሪፖርት የማድረግ የመከላከልና ምላሽ የመስጠት ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ስልጠና ለባለሙያዎቹ በስፋት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
ስልጠናው ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ ስልጠናን (Continous Professional Development Training) ባካተተ መልኩ እንዲጠናቀቅ የኢንስቲትዩቱ የስልጠና ማዕከል የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዳደረገ ከአስተባባሪዎቹ መረዳት የተቻለ ሲሆን ሰልጣኞቹም የነበራቸው ቆይታ መልካም እንደነበረ እና ከዚህ በተግባር ከተደገፈ ስልጠና ብዙ እንደተማሩ እናም ውደመጡበት ተቋም ሲመለሱ ችግሮችን በመረዳት እንዴት በአግባቡ መፍታት እንደሚችሉ የተገነዘቡ መሆናቸውንና ይንንም ለባልደረቦቻቸው እንደሚያካፍሉ አስረድተዋል።