ጥቅምት 07/2017 ስልጤ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን በሰልጤ ዞን የሚቶ ወረዳ የወባ በሽታ አጭር ጊዜ ውስጥ ለመግታት የሚያስችል ወረዳዊ የንቅናቄ መድረክ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሄደ።
የሚቶ ወረዳ ዋና አስተዳደር አቶ ከድር መሀመድ እንደገለፁት የወባ በሽታ መከላከል ስራዎች በተገቢው እንዲከናወን ህብረተሰቡን ያሳተፈ ንቅናቄ ስራዎች እንዲከናወን አሳስበዋል።
ዋና አሰተዳዳሪው በሽታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በሁሉም ቀበሌያት ከወትሮው የተለየ ስትራቴጂ ተቀይሶ ወደ ተግባር መግባት እንደሚገባ ገልፀዋል።
ወባ ወረርሽኝ በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት የህብረተሰብ ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ መሆኑንም አክለዋል።
የሚቶ ወረዳ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፎሌ ሞሳ በበኩላቸው ይህንን አስከፊ በሽታ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ህዝብን በማሳተፍ የመከላከል ስራ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
አክለዉም የማህበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ በየደረጃው የሚገኘው አመራር እና ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዚህ በወባ ወረርሽኝ ሰአት ሁሉም የጤና ባለሙያዎች በትጋት ማህበረሰቡን የወባ መከላከል አካል በማድረግ መስራት እንደሚገባ እንዲሁም ከጤና ኤክስቴንሽን የሚሰጡ መመሪያዎችን በአግባቡ መተግበር እንደሚገባ ገልፀዋል።
የሚቶ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዋበላ ኡስማን በበኩላቸው የወባ በሽታ መከላከል ስራዎች በተገቢው እንደሚከናወንና በዚህ ስራ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የማህበረሰብ ንቅናቄ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚሰራ አመላክተዋል።
በንቅናቄ መድረኩ ላይ አጠቃላይ የወባ በሽታ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያተኮረ የንቅናቄ ሰነድ በወረዳው ጤና ጽ/ቤት የበሽታ መከላከልና ማጎልበት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተሻለ ደሳለኝ በዝርዝር ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።ሲል የሚቶ ወረዳ ኮሚኒኬሽን ዘግቦታል።