የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም ሳምንታዊ የጤና አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ስራዎች ላይ ያተኮረ የበይነ መረብ ውይይት ማካሄዱን የማ/ኢት/ክ/መ/ጤና ቢሮ ገለጸ።
የክልሉ ጤና ቢሮ እና የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የማናጅመንት አካላት እና ባለሙያዎች በተገኙበት የወባ በሽታ ስርጭትን ለመግታት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አስመልክቶ በቀጥታ በበይነ መረብ ከዞን ጤና መምሪያ ሀላፊዎች፣ ከልዩ ወረዳ ጤ/ጽ/ቤት ሀላፊዎች እንዲሁም ባለሙያዎች ጋር ውይይት መደረጉም ታውቋል።
የወባ በሽታ በሳምንቱ 8,813 ኬዝ ሪፖርት መደረጉን እና ከባለፈው ሳምንት 15.8% መቀነሱን እንዲሁም በክልሉ ከምባታ፣ ስልጤ፣ ሀዲያ፣ ሀላባ፣ ጉራጌ ዞኖች ላይ የወባ በሽታ ጫና መኖሩን እና ከነዚህ ውስጥ የከምባታ ዞን 27.7% ላይ እንደሚገኝ የቀረበው ሪፖርት ያስረዳል።
እንደ ክልል 220,000 የቤት ለቤት ጉብኝት ተደርጎ 20,000 ሰዎች የወባ በሽታ እንደተገኘባቸው ፣ 151,000 ሰዎች የወባ ቁጥጥር ስራ ላይ መሰማራታቸውን እና የአጎበር አጠቃቀም 11% መሆኑን እንዲሁም በ31 ወረዳዎች የወባ በሽታ መከ/ኬሚኬል ርጭት ለማድረግ ከተያዘው ዕቅድ በ19 ወረዳዎች የርጭት ስራው እንደተከናወነ እንዲሁም 13,773 ሰዎች የወባ ህክምና ማግኘታቸውን ከቀረበው ሪፖርት መረዳት ተችሏል።
የማ/ኢ/ክ/መ ጤና ቢሮ አቶ ሽመልስ ዋንጎሮ በክልሉ ውስጥ የወባ በሽታ እየጨመረ ያለባቸው አካባቢዎች እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በቅንጅት የሚከወኑ ተግባራትን አጠናክሮ መምራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የወባ በሽታ ተግባራትን ትኩረት ሰጥቶ ከመፈጸም ረገድ በአንዳንድ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች የሚስተዋሉ ጉድለቶች እርምት እንዲደረግባቸው ተናግረዋል።
የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማጠናከር ይገባል ያሉት አቶ ሽመልስ ፣ የወባ በሽታ መከላከያ ዘዴዎችን የማስተማር እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አመላክተዋል ።
የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የተሰሩ ስራዎችን አመሰረት ያደረጉ መረጃዎችን በማጥራት የወባ በሽታ በስፋት እየታየባቸው ባሉ የክልሉ አከባቢዎች የክልሉ ጤና ቢሮ ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመዋል።
የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን የመከላከልና የቁጥጥር ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ በመግለጽ በህገ ወጥ መንገድ ከጤና ተቋማት የሚወጡ መድሀኒቶች ቁጥጥር ስራን በማጠናከር እና የመረጃ ጥራት ላይ ያሉ ጉድለቶችን በማረም የአመራሮችን ተሳትፎ ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የግብአት አቅርቦት እጥረት የሚስተዋልባቸው አከባቢዎች ላይ የግብዓት አቅርቦት ስራውን የማሳለጥ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በቤት ለቤት የሚሰሩ የቅኝት ተግባራት በልዩ ትኩረት ሊፈጸሙ ይገባል ብለዋል።
የማ/ኢት/ክ/መ/ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ሀላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ እንደ ሀገር ብሎም እንደ ክልል የተከሰተው የወባ በሽታ ወረርሽኝ ተግባርን የአመራሩ ቁልፍ አጀንዳ በማድረግ በተከናወኑ ስራዎች የመጡ ውጤቶች መኖራቸውን በማመላከት እንደ ክልል እስከ ሀምሌ 30/2016 ዓ.ም በ70% ለመቀነስ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የአመራሩ፣ የባለድርሻ አካላት እና የማህበረሰቡ ተሳትፎ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዌል።
የመከላከል እና የአካባቢ ቁጥጥር ስራን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ያስገነዘቡት አቶ አሸናፊ የወባ በሽታ ጫና ባለባቸው አካባቢዎች የተጠናከረ የምላሽ ስራ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው የፊት አመራሮች እና በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላትን እያሳተፉ ስራዎችን መፈጸም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የማ/ኢት/ክ/መ/ጤና ቢሮ