በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት ዳይሮክተሬት ጥናትና ምርምር ስነ ምግባር ኮሚቴ /ቦርድ/ ወደ ስራ እንዲገቡ እገዛ የሚያደርግ ስልጠና ለሚመለከታቸው አካላት በወራቤ ዩኒቨረሲቲ ቅጥር ግቢ ዉስጥ እየተሰጠ ይገኛል ።
የማ/ኢ/ክ/ የህ/ጤ/ኢንስትቱዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ለገሰ ጴጥሮስ የስልጠናዉን መድረክ ባስጀመሩበት ወቅት ላይ እንደገለፁት የህብረተሰቡን የጤና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በእዉቀት ላይ የተመሠረተ ጥናትና ምርምር ለመስራት እስከ ታችኛዉ መዋቅር ድረስ በመዉረድ በጋራ እና በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
አቶ ለገሰ አክለዉም የጤና አገልግሎትን ጥራትን ለመጨመር በህብረተሰብ የጤና እክል ላይ ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናት እና ምርምሮችን ማድረግ እንዲሁም በጥናትና ምርምር ዙሪያ ከፍተኛ ልምድ ባላቸዉ ተመራማሪዎች ወቅቱን የጠበቀ ተከታታይ የአቅም ግንባታ ስራዎችን በመስጠት በርካታ ለዉጦችን ማስመዝገብ ይቻላል ብለዋል።
ዶክተር ሰራዊት ሀንዲሶ በትም/ሚኒሰቴር የጥናትና ምርምር የማህበረሰብ ትስስር ጉዳዮች ሀላፊ የስልጠናውን ሰነድ ባቀረቡበት ወቅት ላይ እንደተናገሩት ጥራት ያለዉ ጥናትና ምርምር ለማድረግ በቂ እዉቀት ማምረት እና መፍጠር እንዳለብን ገልፀው በርካታ መረጃዎችን ለማደራጀት ሁላችንም የጋራ የሆነ እቅድ በማዘጋጀት በመተጋገዝ እና በመረዳዳት ተናበን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
እንደ ዶ/ር ሰራዊት ገለፃ ጥናትና ምርምር ስናደርግ የዜጎችን የጤና ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ባሻገር የህብረተሰቡን አንድነት ፣እኩልነት ፣ባህላቸዉን፣ማንነታቸውን እንዲሁም መብቶቻቸውን በማይነካ መልኩ መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል።
በስልጠናው ላይ የሀገር አቀፍ ጥናትና ምርምር ስነምግባር ገምጋሚ ኮሚቴ ቦርድ አባላትን ጨምሮ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ፣የክልሉ ፖሊሲና ጥናትና ምርምር ተቋም፣የዋቻሞ፣ የወልቂጤና ወራቤ ዩኒቨርስቲ ተወካዮች እንዲሁም የሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ የክልሉ ጤና ቢሮ የማኔጅመንት አባላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ስልጠናው በነገው ዕለትም እንደሚቀጥል ተገልጿል ።
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ