Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ በተገኙበት የሃገር ውስጥ የህክምና ግብአት ምርት እና ኢኖቬሽን አውደ-ርእይ ተከፈተ

በሃገራችን የመጀመሪያ የሆነው የሃገር ውስጥ የህክምና ግብአት እና ምርቶች ኢኖቬሽን አውደ-ርእይ “ጤናችን በምርታችን” በሚል መሪ ቃል መካሄድ ጀምሯል፡፡

በግርብናው ዘርፍ የተገኘውን የሃገር ውስጥ ምርት የማሳደግ ስኬት የህክምና ግብአት እና ምርትንም በማሳደግ ይደገማል ያሉት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ የሃገር ውስጥ የህክምና ምርቶችን ማሳደግ አስፈላጊነትን በተመለከተም የኮቪድ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሃገራት ክትባትንና ሌሎች ግብኣቶችን ማግኘት መቸገራቸውን በማስታወስ ከዚህ ቀደም ከሀገር ዉስጥ አምራቾች ሲቀርብ የነበረዉ የህክምና ግብኣት 8 በመቶ ብቻ የነበረዉ አሁን ላይ ወደ 36 ፐርሰት በጥቂት አመታት ውስጥ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የሃገራችን የህክምና ምርቶች ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ በዘርፉ አቅም ያላቸው ግለሰቦች ቢሳተፉ ትርፋማ እንደሚሆኑ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ እንደ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዘመናት የባህል መድሃኒት እውቀት ያላት ሃገር በመድሃኒት ምርት ከራሷ አልፋ ለሌሎች ሃገራትም መትረፍ ትችላለች ብለዋል፡፡

ጊዜው ክረምት በመሆኑ በተለይም ኢትዮጵያውያን ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ አውደ-ርእዩ በማምጣት እና በማስጎብኘት የልጆቻቸውን ተነሳሽነት እንዲያሳድጉ ጥሪ ያቀረቡት ዶ/ር አብይ፤ አውደ ርእዩን ያሰናዳው ጤና ሚስቴር እንዲሁም መድሃኒት በማምረት የዜጎችን ህይወት በመታደግ ላይ ለሚገኙ አምራቾች ምስጋና በማቅረብ የኢትዮጵያ መንግስትም ለዘርፉ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል፡፡

ጤና ሚኒስቴር የሃገር ውስጥ የህክምና ግብአት እና ምርትን ማሳደግን በፖሊሲው ውስጥ አካቶ እየተገበረ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በአውደ-ርእዩ መክፈቻ የተናገሩ ሲሆን፤ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የሃገር ውስጥ የመድሃኒትና ሌሎች ግብአቶች ምርትን ማሳደግ መሆኑን በመግለጽ አዳዲስ ምርቶችን በማምረት ወደ ገበያ እንዲገቡ ለባለሃብቶች ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው አውደ ርእዩ ከ110 በላይ የሃገር ውስጥ የህክምና ግብአቶች እና ምርቶች አምራቾች የተሳተፉ ሲሆን፤ አውደ ርእዩ ለቀጣይ ስድስት ቀናት ለህዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *