የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ በተመለከተ በሳምንቱ ዉስጥ የተከናወኑ የቅኝትና ምላሽ አሰጣጥ ተግባራት ቀርበው ሰፊ ዉይይት ተደርጎባቸዋል ።
አቶ አገኘዉ ፀጋዬ የቢሮው ጤናና ጤና ነክ አደጋዎች ቅኝት ምላሽ ዳይሬክቶሬት ባለሙያ የሳምንቱን ሪፖርት ሲያቀርቡ በዚህ ሳምንት 5176 የወባ በሽታ መከሰቱን ጠቁመዋል ።
በክልሉ በሳምንቱ ከምባታ ዞን ቃጫ ቢራ ወረዳ 604 ሰዎች ወይም 27 በመቶ በወባ በሽታ ከፍተኛ ቁጥር ማስመዝገባቸው የተገለፀ ሲሆን በሳምንቱ 26 ሰዎች በተለያዩ ተቋማት ተኝተው እየታከሙ መሆኑም ተገልጿል።
በሳምንቱ ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት 455 በከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጎዱ ወገኖች ሪፖርት መደረጉን የገለፁት አቶ አገኘዉ 13 የሚሆኑት ሰዎች በተለያዩ ተቋማት ላይ በምግብ እጥረት ምክንያት ተኝተው እየታከሙ መሆናቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በሪፖርቱ 16 የጨቅላ ህፃናት ሞት የተመዘገበ ሲሆን 177 የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የደም ተቅማጥ፣131 የደም ግፊት፣ 39 የሚሆኑት ደግሞ ለስኳር በሽታ ተጋላጭ መሆናቸዉ ተጠቁሟል ።
አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ የጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊና የፕሮግራሞች ዘርፍ ሀላፊ በዉይይቱ መድረክ ላይ እንደተናገሩት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በየጊዜው እየጨመረ የመጣዉን የወባ በሽታ ለመግታት እና ዜጎች እንዳይሞቱ ለማድረግ መከላከልን መሠረት ያደረገ ጥንቃቄዎችን በማድረግ የወባ ጫናን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ይገባል ብለዋል።
አቶ ማሙሽ ሁሴን የማ/ኢ/ክ/ የህ/ጤ/ኢንስትቱዩት ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸዉ በክልሉ የወባ በሽታ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን ገልፀው የስርጭት መጠኑ ከተማዎች ላይ ይበልጥ መስተዋሉን ጠቁመዋል ።
አቶ ማሙሽ አክለውም የወባ በሽታ ለክልሉ ከፍተኛ ስጋት እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰዉ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ክልል አቀፍ እቅድ በማዘጋጀት የህብረተሰቡን የግንዛቤ አቅም በማሳደግ እና ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሁሉም በጋራ መረባረብ እንደሚገባ አስረድተዋል ።
የቢሮው ጤናና ጤና ነክ አደጋዎች ቅኝት ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወልደሰንበት ሸዋለም የዚህን ሳምንት ቅኝት ሲያብራሩ የወባ እና የኩፍኝ በሽታ ስርጭቱ ከባለፈው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር መጠነኛ መሻሻሎች ቢታዪበትም ችግሩን ይበልጥ ለመቀነስ በቀጣይ ከፍተኛ ስራ ይጠበቅብናል ብለዋል ።
አቶ አብድልፈታ ሙደስር በክልሉ ህ/ጤ/ኢ የላብራቶሪ ባለሙያ ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ በክልሉ አንዳንድ አከባቢዎች የዉሃ አሰሳ ባደረጉበት ወቅት ላይ 81 የሚሆኑ ናሙና ተወስዶ 62 ናሙና ላይ በተለያዩ መልኩ የሽንት ቤት ባክቴሪያ አንደተገኘበት ጠቁመው በዚህ ምክንያት ዉሃዉ በመበከሉ ለመጠጥነት እንደማያገለግል ገልፀዋል ።
በየቤቱ የሚገኘዉ የዉሃ ቧንቧ ሰዎች ሜዳ በሚፀዳዱበት ጊዜ በቁፋሮና በተለያየ መስመር ዝርጋታ ጊዜ ቆሻሻዉ ወደ ዋናዉ ታንከር ስለሚገባ በቀላሉ ይበክላል ።ስለዚህ ህብረተሰቡ ዉሃ ላይ ያለዉን ከፍተኛ ችግር በመገንዘብ ዉሀን ከተቻለ አክሞ ካልሆነ ደግሞ አፍልቶ በመጠቀም ከተለያዩ በሽታዎች ራሳቸዉን መጠበቅ ይገባል ብለዋል አቶ አብድል ፈታ ።
በመጨረሻም ከዞኖች ጋር በወባ በሽታና በሌሎች የድንገተኛ ጤና አደጋዎች ላይ ያተኮረ በሳምንቱ የተሰሩ ስራዎችን ቀጥታ የቪዲዮ ሪፖርት ከተሰማ በኃላ በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ዉይይት ተደርጎባቸዉ ዉይይቱ ተጠናቋል