Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ እየተከሰተ ባለው የጎርፍ አደጋ ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ስጋቶችን ቀድሞ መከላከል እንደሚገባ ተገለጸ።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መደበኛ የወረርሽኞች መቆጣጠሪያ ማዕከል (Emergency Operation Center – EOC) የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ሳምንት ( WHO week 19) ግምገማ ተደርጓል፡፡

ሳምንታዊ የተጠቃለለ የበሽታዎች ክስተት፣ ቅኝትና ምላሽ አሰጣጥ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን በክልሉ እየተከሰተ ያለው የጎርፍ አደጋ አሳሳቢ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በድንገት ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ውይይት በማድረግ የወባ በሽታ በአንዳንድ ዞኖችና ወረዳዎች ጭማሪ በማሳየቱ የመከላከልና የቁጥጥር ተግባራትን በማጠናከር እንዲሁም የአጎበር አጠቃቀም ላይ ያሉ ጉድለቶችን በማረም ረገድ የውይይት መድረኩ አጽንኦት ሰጥቶ መክሮበታል።

የኮሌራ በሽታ ስጋት ሆኖ እንዳይቀጥል የቅድመ ማስጠንቀቅና የመከላከል ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የተጠቆመ ሲሆን ከፍተኛ አጣዳፊ የምግብ እጥረት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ልዩ ትኩረት በመስጠት ክትትል ሊደረግ እንደሚገባ ተገልጿል።

ውይይቱን የመሩት የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በክልሉ የወባ በሽታ፣ በከፍተኛ ሁኔታ ያለባቸው ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ማህበረሰቡ ላይ አስከፊ የሆነ የጤና ጉዳት ከመድረሱ በፊት ለመቆጣጠር እና ለመመከት የሚያስችል ተግባር ሊፈጽሙ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኮሌራ እንዲሁም የምግብ እጥረት ችግርን ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት በተከናወኑ ተግባራት የበሽታውን ስርጭት በተወሰነ መልኩ መቀነስ መቻሉን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ በተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች የሚስተዋለው ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በየደረጃው ያሉ አመራሮችና በለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ተግባሩን ሊመሩት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ከወባ ወረርሽኝ አንፃር ትኩረት ከሚሹ አካባቢዎች ከምባታ፣ ጉራጌ፣ ዞኖች እንዲሁም ጠምባሮ ልዩ ወረዳ ላይ በሳምንቱ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ ማሙሽ ከምግብ እጥረት ልየታና ክትትል ስራዎች አኳያ የም ዞን እና ጠምባሮ ልዩ ወረዳ ልዩ ክትትል ማድረግ እንደሚገባ በማመላከት ሌሎች ትኩረት የሚሹ አካባቢዎችን በመለየት የድጋፍ እና ክትትል ተግባራትን በማሳለጥ የማህበረሰብ ግንዛቤ የማሳደግ እና የቅድመ ጥንቃቄ መልእክቶች እንዲተላለፋ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

በዞን ያሉ ከፍተኛ አመራሮችና በየደረጃው ያሉ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክኒያት የሚከሰቱ ድንገተኛ ወረርሽኞች በማህበረሰቡ ላይ የጤና ጉዳት፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከማድረሳቸው በፊት ለመቀልበስ የማያስችል ተግባር በመፈጸም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አቶ ማሙሽ ጠይቀዋል።

የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ለገሰ ጴጥሮስ በበኩላቸው ችግር ፈቺ የሆነ የምላሽ ስራ በመስራት በጉድለት በተለዩ ጉዳዮች ላይ ዕቅድ አውጥቶ ወረርሽኝ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ወቅታዊ ግብረ መልሶችን በመስጠት የጎርፍ አደጋውን ተከትሎ የሚከሰቱ ወረርሽኞችን ለመመከት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ተገቢ ነው ብለዋል።

የማ/ኢት/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *