በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እያጋጠሙ ያሉና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ክስተቶች፣ በወረርሽኝ መልክ የሚከሰቱ የጤና ስጋቶችን አስቀድሞ ለመከላከል የድንተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ አሰጣጥ ስርአትን ይበልጥ ማጠናከር ተገቢ መሆኑን ነዉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ማስባበሪያ ማዕከል /EOC/ በሳምንታዊ የአፈፃፀም ግምገማዉ ላይ የተብራራዉ ፡፡
በክልሉ ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት፣ወራት እንዲሁም ካለፈዉ አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር በንፅፅር የታዩ የወረርሽኝ ክስተቶች፣ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሁኔታ በዝርዝር በቀረበዉ ሪፖርት የተመላከተ ሲሆን በተለይም በግንባር ቀደምነት ከተነሱና ሰፊ ዉይይት ከተደረገባቸዉ አበይት ጉዳዮች መካከል የወባ በሽታ ስርጭት ፣የኩፍኝና የኮሌራ ወረርሽኝ ክስተት፣ዉስብስብ የሆነ የስርአተ ምግብ ችግር፣የማጅራት ገትር ፣ የተቅማጥ በሽታ እንዲሁም እንደ ቲቢና ኤች. አይ.ቪ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች እና በአሁኑ ወቅት እጅግ አሳሳቢ እየሆኑ የመጡት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አሳሳቢነት ላይ የማስተባበሪያ ማዕከሉ በጥልቀት ገምግሟል ፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን ዉይይቱን በመሩበት ወቅት ባስቀመጡት አቅጣጫ ላይ እንዳብራሩት በየሳምንቱ በኢኒስቲትዩቱ በየሳምንቱ የሚገመገሙ የድንገተኛ አደጋ ስጋቶችና ክስተቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ የመጡበት ሂደት መኖሩን በመግለፅ በተለይም የወባ ጫናን ለመቀነስ በተሰራዉ ሰፊ ስራ በአብዛኛዉ ወረዳዎች ከባለፈዉ አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ አፈፃፀም ቢኖርም በክልሉ አንዳንድ ወረዳዎች ላይ ለአብነትም እንደ ምስራቅ ባድዋቾ፣ሀደሮ ጡንጦና ወልቂጤ ከተማ ያሉ አካባቢዎች በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረበት ሂደት ልዩ ትኩረትና የተጠናከረ የምላሽ አሰጣጥ ስርአት የሚያስፈልገዉ በመሆኑ ወደ ታች ወርደዉ እየደገፉ ካሉ ባለሙያዎች በተጨማሪ የግብአትና ተጨማሪ ድጋፍ የሚያስፈልግ መሆኑን በአፅንኦት ተናግረዉ ይህንንና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ የአመራሩ ሚና በየደረጃ ሊጎለብት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ በክልሉ የሚተገበሩ የጤናና ጤና ነክ ተግባራት በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረቱ ሊሆኑ እንደሚገባና በጠራ መረጃ ላይ የተመሰረተ የግብአት ስርጭት እንደሚያስፈልግም ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡
የእለቱ የድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ማስባበሪያ ማዕከል /EOC/ አባላት ባነሱት ሀሳብ የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የሚከናወኑ ተግባራት በተለይም በጤና ተቋም የሚሰጡ አገልግሎቶች ትኩረት እንደሚሹ፣ በጥናት ለተለዩ ችግሮች ፈጣን ምላሽ የሚያስፈልጋቸዉ መሆኑ፣ ለላቦራቶሪ ባለሙያዎች ቀጣይነት ያለዉ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መስጠት፣የክትባት አገልግሎት ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን በየደረጃዉ ማረም እንዲሁም በቲቢ፣ ኤች.አይ.ቪና ተላላፊ ያልሆኑ በሽዎች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመዘገበ ያለዉ ከፍ ያለ ቁጥር አሳሳቢነት ላይ የጤና ተግባቦትና የማህበረሰብ ንቅናቄ መፍጠር ስራ ኢኒስትቱዩቱ በቀጣይ አጽንኦት ሰጥቶ የሚሰራባቸዉ ተግባራት ሊሆኑ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጤና ቢሮ
One Response
It is promising that the institute is working by considering the current circumstances of the region’s public health important diseases mitigation, response, capacity buildings and resources decentralization.
Keep it up!!