በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት የሚከሰቱ ወረርሽኞች የማህበረሰብ የጤና ስጋት እንዳይሆኑ መደበኛ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የ6 ወራት አፈጻጸም ግምገማዉን በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
በዚሁ ጊዜ የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ምክር ቤት ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ግዛቸው ዋሌራ ባስተላለፉት መልዕክት ባለፉት ጊዜያት ጥራት ያለው የላቦራቶሪ መረጃን ለውሳኔ በመጠቀም ረገድ የተከናወኑ ተግባራት እንደ ሀገር ብሎም እንደ ክልል የማህበረሰቡን የጤና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት የሚከሰቱ ወረርሽኞችን ፈጥኖ ከመቆጣጠር አኳያ ጉልህ ፋይዳ እንደነበረው ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቀጣይም የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚከሰቱ ድንገተኛ የጤና አደጋዎች በእናቶች እና ህጻናት እንዲሁም በህብረተሰቡ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን የጤና ቀውስ ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ እገዛ ለማድረግ የክልሉ ምክር ቤት ቁርጠኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የህበረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በመልዕክታቸው ማህበረሰቡን ከየትኛውም የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ የጤና ስጋቶች ለመከላከል ከመደበኛ የጤና ተግባራት ጎን ለጎን በማህበረሰቡ ላይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ከማሳደሩ በፊት የበሽታ ሁኔታዎችን ክስተት ቀድሞ በመተንበይ የመቀልበሻ አቅጣጫዎች በመዘርጋት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
በ2016 ዓ.ም በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ሊከሰቱ የሚችሉ የወረርሽኝ አደጋዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመተንበይ የዝግጁነትና ምላሽ ዕቅዶችን በማዘጋጀት ወደ ተግባር መገባቱን የጠቆሙት አቶ ማሙሽ በግማሽ ዓመቱ የወባ፣ የኮሌራ፣ የኩፍኝ በሽታ፣ ያልተመጣጠነ የምግብ እጥረት፣ የጎርፍ፣ የእሳት ቃጠሎ በተከሰተበት ወቅት ፈጣን ምላሽ መስጠት መቻሉን አመላክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በክልሉ በድንገት የሚከሰቱ ወረርሽኞችን በመከላከል ረገድ በክልሉ ም/ር/መስተዳድር የሚመራው የአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት ማዕከል ያደረገው እገዛ ማህበረሰቡ ላይ የከፋ የጤና አደጋ እንዳይከሰት ማድረጉን የጠቀሱት ሀላፊው ባለፉት 6 ወራት ወርሽኞችን በስታንዳርድ መሰረት ፈጥኖ ያለመለየትና ፈጣን ምላሽ ያለመስጠት፣ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ያለማጠናከር፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ትኩረት ማነስ፣የሰው ሀይል አለመሟላት እንዲሁም የበጀት እጥረት ችግሮች ማጋጠሙን በመግለጽ ታዓማኒና ጥራት ያለው የላቦራቶሪ ውጤት ያለማግኘት፣ የላብራቶሪ ግብዓት አስተዳደር ላይ ጉድለት መኖር፣ የናሙና ቅብብሎሽ ክትትል ችግር፣ የላብራቶሪ አገልግሎት ዘርፍን በአግባቡ ያለመደገፍ፣ ለላብራቶሪ ዘርፍ በቂ በጀት ያለመመደብ ችግሮች ማጋጠማቸውንም አክለው ገልጸዋል።
በዚህ የሁለት ቀናት የግምገማና የምክክር መድረክ ፍሬያማ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ